Partly Cloudy Partly Cloudy Sunny
18C 26C 25C
ክስኞ ሮብ

የትያትርና ባሕል አዳራሽ

Theater and Cultural Hallበፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ቀደም ብሎ ተቋቁሞ የነበረው የሀገር ፍቅር ማህበር በአቶ መኮንን ሀ/ወልድ አማካኝነት ሲመሰረት በጊዜው ሥልጣን ለስደተኞችና ለባንዳዎች መሰጠቱ በስደተኞችና በአርበኞች መካከል አያሌ መቃቃሮች ተፈጠረ፡፡  ይኸውም የሀገር ፍቅር ማህበር የስደተኞች ቅስቀሣና ዲስኩር ማስተጋቢያ በመሆኑ ከዚህ ሁኔታ ለመሸሽ አርበኞች ህዝብ ይደግፋቸው ነበርና የእነሱን ሀሣብ ለመግለጽ የቴአትር ጥበብን ለማስፋፋት ታሪክ ሰርተው ያለፉትን አርበኞች ስማቸውን ከመቃብር በላይ ለማዋል የአርበኝነቱን ታሪክ አጉልቶ ለማውጣት በ1939 ዓ.ም. አርበኞች ተሰባስበው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥር በጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽ/ቤት የሚተዳደር አንድ ኮሚቴ በዮፍታሄ ንጉሴ ኃላፊነት አቋቋሙ፡፡ ሆኖም ገና በጀምሩ ገጣሚ፣ ባለቅኔ፣ የቴአትር ደራሲና አርበኛ የነበሩት ዮፍታሄ ንጉሴ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ ሥራው ኮሚቴውን በመሰረቱት ሰዎች ላይ ይጣላል፡፡ ይህ የቴአትርና ሙዚቃ ክፍል አራት ኪሎ በሚገኘው ጀግኖች ማህበር ጽ/ቤት ውስጥ የቴአትር ማስፋፊያ ጽ/ቤት በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥር ሆኖ ነሐሴ 19 ቀን 1939 ዓ.ም. ተቋቋመ በመጀመሪያ የታየው ቴአትር "መቀነቷን ትፍታ " ሲሆን ይህንን ቴአትር በነሐሴ ወር ካሣዩ በኋላ በ194ዐ ዓ.ም. የበፊቱን ቦታ ለቆ አዲስ አበባ አራዳ ፍ/ቤት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው ቅጥር ግቢ ውስጥ በወቅቱ አዲስ አበባ አውራጃ ፍ/ቤት ተዛውረዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ግዜ ደመወዝ ይጨመር በማለት አስተዳደሩን ያስጨንቁት ስለነበር ጥያቄያቸውን ከቁጥር ባለማስገባት ከነጭራሹ እንዲባረሩ ተደረገ፡፡ 1948 ዓ.ም. ለንጉሱ 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ አዲስ ቤተ-ተውኔት ቀ.ኃ.ሥ ቴአትር እንደሚከፈት ሲታወቅ ያባረሩዋቸውን አርቲስቶች በማሰባሰብ ቀጠሯቸው፡፡ ይኸውም ማ/ቤት የራሱን ቴአትር ለማቋቋም ሳይሆን ቀ.ኃ.ሥ ቴአትርን ለመክፈት ስለነበረ አርቲስቶች ከነሙዚቃ መሣሪያቻው ወደእዛ ተላኩ፡፡

በ1948 ዓ.ም. የተዘጋው የማዘጋጃ ቴአትር ለቴአትርና ለሙዚቃ ትኩረት ሳይሰጥ እስከ 1958 ዓ.ም. ቆየ በዚህ ወቅት ማዘጋጃ ቤቱን በወቅቱ በከንቲባነት ይመሩት የነበሩት የተከበሩ ቢትወደድ ዘውዴ ገ/ህይወት ነበሩ በዚሁ መሥሪያ ቤት ውስጥም በህዝብ ግንኙት ክፍል በዳይሬክተርነት ማእረግ አቶ ታደሰ ወርቁ ይመሩት ነበር፡፡ እኚህ ሰው ከእለታት አንድ ቀን ራእይ ይታያቸዋል፡፡ ይህ ራእያቸው በማዘጋጃ ቤቱ ስር የሚመራ አንድ የሙዚቃ ክፍል የማቋቋም አስፈላኒቱ ነበር፡፡ ይህም ሀሣባቸው ሳይውል ሳያድር ለአዲስ አበባ ከተማ ልማትና እድገት ለከተማ ነዋሪው በነፃ የማዝናናትና የማስተማር እቅድ በመንደፍ ሙዚቃ ክፍል መቋቋም እንዳለበት በዝርዝር አሳማኝ ነጠቦችን በማካተት ማስታወሻቸውን ለክቡር ከንቲባው እንዲፈቅዱላቸው አቀረቡ፡፡ ክቡር ከንቲባውም የቀረበው ሀሣብ ቅንና አሳማኝ መሆኑን በመረዳት ክፍሉ እንዲቋቋም ፈቀዱላቸው ከዚህ በኋላ አቶ ታደሰ ወርቁ የቅጥር ምልመላ በወጣት የተነገባ እንዲሆን በማሰባቸው 1ዐ ወጣት ልጃገረዶችንና 5ዐ ወጣት ወንዶችን በጠቅላላው 6ዐ ሙዚቀኞችን በሙዚቃ ሙያ እንዲሰለጥኑ ለአዲስ አበባ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሙዚቀኛ ክፍል ትብብር ጠይቀው ለአንድ ዓመት ሥልጠና ለመስጠት በመፈቀዱ በ1959 ዓ.ም. ትምህርታቸውን ሰልጣኞቹ መከታተል ጀመሩ ከዚህ በኋላ በ196ዐ ዓ.ም. የተሰጣቸውን ኮርስ አጠናቀው በከንቲባ ዘውዴ ገ/ህይወት እንዲመረቁ ተደረገ፡፡ ይህም ወቅት አርቲስ ፋንቱ ማንዶዬ ሲያስታውሰው "የወጣትነት ጉልበት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያስገነዘበኝ እለት ነው በወቅቱ እኔ ድራሜጀር ነበርኩኝ የአዲስ አበባ ህዝብ አጅቦን ከአዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ማለትም ምኒልክ አደባባይ ተነስተን ቁልቁል በአሮጌው ፖስታ ቤት ስንወርድ ይከተለን በነበረው የሙዚቃ አፍቃሪ ታጅበን የቸርቸር ጐዳናን ቁልቁል ስንሄድ የነበረኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ ያሁኑን ሲኒማ አምባሳደር ወደኋላ በመተው መስቀል አደባባይ እንደት እንደደረስን አላስታውስም በሰው ጭብጨባና ደስታ የላይኛውን ቤተመንግሥት አቋርጠን ስድስት ኪሎ አካባቢ ቆመን ሙዚቃውን ስናቀርብ ለእኔ የ3 ደቂቃ ጉዞ እንኳን ያደረኩ አልመሰለኝም ምን ጊዜም የምትወደው ሙያ ውስጥ መኖርን የመሰለ ምን አስደሣች ነገር አለ ብሏል፡፡

ከተመረጡም በኋላ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃና የቴአትር ክፍል በሚባል ተሰይሞ እንቅስቃሴውን በድሮ ማዘጋጃ ቤት በአሁኑ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሆነው ግቢ ውስጥ የሙዚቃ ክፍሉ ሥራውን ጀመረ ይህም የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ መሠረት የተጣለበት ዘመን ነበር ለዚህም የሙዚቃ ክፍል በኃላፊነትና በአቀናባሪነት አቶ ተፈራ አቡነወልድ ሲመደቡ በባህል ሙዚቃ አሰልጣኝነት አቶ ለማ ገብረህይወትን እንዲሁም ቀልዶችንና አጫጭር ቴአትሮችን አሰልጣኝ በመሆን አቶ ሳህሉ አዝነህን እንዲቀጠሩ ሆኖ ሙያዊ ሥራውም እንቅስቃሴውን ጀመረ፡፡ የዚህን ወቅት እንቅስቃሴ አጀማመር ተፈራ በላቸው ሲያስታውሱን..

"አስተማሪያችን መልካም አባቶቻችን ነበሩ ከሁሉም የማልረሳው ሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ሲመድቡን የእጅ አንጓች አቀማመጥና የከንፈር ይዘትን በማየት ነበር ምን የህል አዋቂዎች እንደነበሩ ነው የማስታውሰው" ብለዋል፡፡

በዚያን ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና አውራ መንገዶች በመስፋፋት ላይ ነበሩ ለአብነትም የህል እንደ አስመራ መንገድ፣ የበላይ ዘለቀ መንገድ፣ የቸርቸር ጐዳና  መንገድ፣ ግራና ቀኝ በተተከሉ መብራቶች በመድመቃቸውና በማሸብረቃቸው በጊዜው በማስደነቃቸው ይህኑ የከተማ ውበት በግጥም፣ በዜማ፣ በሙዚቃ ተዋህዶ በአቶ ተፈራ አቡነወልድ ደራሲነትና አቀናባሪነት ለወቅቱ የሚሆን አደይ አበባ አዲስ አበባ በተሰኘ ዜማ ሙዚቃ ክፍሉ የመጀመሪያ ብቃቱን ለህዝብ አቀረበ፡፡ በዚሁም እንቅስቃሴው እየቀጠለ ሄዶ በመሀሉም ክቡር ከንቲባው ወደ ሌላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተዛውረው ሲሄዱ በምትካቸው ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ በከንቲባነት በተመደቡ ከአንድ ዓመት ቆይታቸው በኋላ በራሳቸው ዲዛይንና ፈጠራ የለገዳዲ ግድብን አሰሩ በዚህ የምርቃት በዓል ላይም የሙዚቃ ክፍሉ የሞቀና የደመቀ የፋንፋር ሙዚቃ ከማሰማቱም ሌላ በአቶ ተፈራ አቡነወልድ አማካኝነት የተዘጋጀ ዜማ " የለገዳዲ ግድብ ዝናው ይሰማ በዓለም" በሚል ህብረ ዝማሬ ለህዝብ አስደምጧል፡፡ ሙዚቃ ክፍሉ እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ በመቀጠል በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ጽዳትን፣ ልማትን፣ጤናን አስመልክቶ ቅስቀሣ ይደረግ ስለነበር በዚያን ጊዜ አጠራር በሰሜን ማዘጋጃ ቤት፣ በደቡብ ማዘጋጃ ቤት ለምእራብና ለምስራቅ እንዲሁም ለመሀል ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነዋሪዎች በየሣምንቱ ለመቀስቀስና ለማስተማር ለማዝናናትም ጭምር ሙዚቃ ክፍሉ እየተዘዋወረ " ሙዚቃ ለአይምሮ ትምህርት ለኑሮ " በሚለው መርህ ሥር በየት/ቤቱ እየተዘዋወረ እያነቃቃና እያስተማረ ሲሳተፍ ነበር፡፡

ከጥቂት ዘመናት በኋላ በሀገራችን የመንግስት ለውጥ በመደረጉ ማዘጋጃ ቤቱን በከንቲባነት ኢንጂነር መኮንን ሙላቱ እንዲመሩት ተደረገ በዚያን ወቅት የሙዚቃ ክፍሉ ባቀረበው የይገባኛል ጥያቄ መሠረት የማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ በውጭ ሀገር ዜጋ ተይዞ የነበረ በመሆኑ ሲቲ ሆል ሲኒማ ቤት አዳራሽን ተረክቦ በአዲስ መልክ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሙዚቃ ክፍል ተብሎ በመሰየም በዋና ሥራ አስኪያጅነት በ1967 ዓ.ም. አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ ተመድበው በመንቀሣቀስ የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት ቴአተር ቤቱን እንደ ቴአትር ቤት ማደራጀት ስለነበረባቸው ያልተሟላውን የቴአትር ክፍልና የባህል ሙዚቃ ቡድንን ማደራጀት ሲሆን በቅድሚያ ግን ተዋንያኑን በመቅጠር ማሟላት ነበር፡፡

27 ተዋንያንም ተቀጠሩ፡፡ ይህንኑ አሟልተው ቴአትርን በቴአትር ቤት ውስጥ መሠረት ጣሉ፡፡ ይኸው ቴአትር ቤት የባህል ሙዚቀኞች ያልነበሩት በመሆኑ በቀድሞ አጠራራቸው ኦኬሰትራ ኢትዮጵያ ተብለው የሚጠሩት የባህል ቡድኖት በወቅቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ትዕዛዝ በ1968 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቴአትርና ባህል አዳራሽ ጋር እንዲቀላቀሉ ትዕዛዝ በመስጠቱ የባህል ቡድን ኃላፊ በመሆን አቶ ተስፋዬ ለማ እንዲመሩት ሆኖ ከተዛወሩበት ጊዜ ጀምር ባህላዊ፡ ትምህርታዊና አዝናኝ ሥራዎችን ለህዝብ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በዚያው ዘመን የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ የአቶ መንግሥቱ ለማ ድርሰት " ባለካባና ባለዳባ" የተሰኘውን ድራማ አዘጋጅተው ለህዝብ አቀረቡ፡፡ ከእሳቸው በኋላም አቶ አባተ መኩሪያ ተመድበው በመምጣት ቴአትር ቤቱን ላቅ ወዳለ ደረጃ አድርሰውታል፡፡ ከአዘጋጃቸው ሥራዎች መካከል የአቶ አያልነህ ሙላት ድርሰት " እሳት ሲነድ" "የመንታ  እናት" ሲሆኑ ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ድርሰቶች " አቡጊዳ ቀይሶ "፣ " መልዕክተ ወዛደር"፣ "መቅድም"፣ "ኦቴሎ" እና "ቴድሮስ" ወዘተ… ይገኙበታል፡፡ በተጓዳኝም በባህል ሙዚቃ የተዘጋጀ " እዝለ ጥበባት" የተሰኘ ኘሮግራም ለህዝብ ቀርቦ አንድ አመት ከ6 ወር ታይቷል፡፡ በዘመናዊ ሙዚቃም " ጤና ያጣ ፍቅር" የተሰኘው የአቶ ተፈራ አቡነወልድ ሙዚቃዊ ድራማ ድርሰት በአርቲስት ሥዩም ተፈራ ተዘጋጅቶ ለረዥም ጊዜ ለህዝብ እይታ ቀርቧል፡፡ ምን የህል ሙዚቃዊ ድራማዎች እንደቀረቡ አቶ ተፈራ አቡነወልድ ለተጠየቁት ሲመልሱ…..

"ቅዳሜ እግሬ" ፣ "እመሪ ቤቴ" ፣ "የጠላ ሻጯ ልጅ" ፣ "የት ሄደሽ ነበር" እና " የአዲስ አበባ ኮረዳ" የማስታውቸው ሲሆን አኔ ደርሼ በሙዚቃ ያቀናበርኳቸው ናቸው፡፡"
ከእነዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ቅርጽ በአንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች በርካታ ሥራዎች ለህዝብ ቀርበዋል፡፡ " መቃብር ቆፋሪ"፣ "የሊስትሮ ኦፔራ" ፣ "ታርትዮፍ"፣ "ያላቻ ጋብቻ" ፣ "ጂሊየስ ቄሣር" ፣ "ስመኝ ስንት አየሁ"፣ " ወጥመድ" ፣ "የሚተኑ አበቦች ፣ "የከርቸሌው ዘፋኝ" ፣ "የመጨረሻው ህልም" ፣ " ቆንጆዎቹ" ፣ " ዳና " ፣ "ሶስና" ፣ "የታፈነ ጩኸት" ፣ " አንድ ክረምት" ፣ " ጣይቱ" እና የመሣሰሉት ተውኔቶች ለቴአትር ታዳሚው ቀርበው ከፍተኛ አድናቆት አትርፈዋል፡፡
ከአቶ አባተ መኩሪያ በኋላ ቴአትር ቤቱ ለተወሰኑ ወራቶች ወ/ሮ ጀማነሽ ሰለሞን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩት ቆይተው በኋላም በምትካቸው በዋና ሥራ አስኪየጅ አቶ ጌታቸው ታረቀኝ ለተወሰኑ አመታቶች ቴአትር ቤቱን መርተዋል፡፡ ከአቶ ጌታቸው ታረቀኝ በኋላም አቶ በኃይሉ መንገሻ ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሥራ አስኪያጅነት ቴአትር ቤቱን የሚመሩት አቶ ቶማስ ቶራ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ቴአትር ቤት የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አደራሽ በመባል መሠረት የተጣለበት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃና የቴአትር ክፍል ከተቋቋመበት 196ዐ ዓ.ም. ጀምሮ 4ዐኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡

የባህልና የቱሪዝም ሀብቶቻችን
በከተማችን ልማት ውስጥ
ግንባር ቀደም ተዋናዮች እንዲሆኑ
እንሰራለን፡፡

         
Developed by JoomVision.com

መረጃዎች እንድንልክልዎ ይመዝገቡ