የቴአትር ቤቱ አጭር መግለጫ ፣
የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ከመቋቋሙ በፊት በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በነበረው የስነጥበባትና ቴአትር መምሪያ ስር በ1973 ዓ.ም በህፃናት ቴአትር ክፍልነት ተቋቋመ፡፡ በ1977 ዓ.ም መጨረሻ ይኸው ክፍል ወደ ህፃናት መዝናኛና ማበልፀጊያ ተለውጦ ለአራት ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን በመቆየት ነሀሴ 13/1981 ዓ.ም የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በመባል በአዲስ መልክ ሊደራጅ ችሏል፡፡
በዚህ መልክ እየተደራጀ የነበረው ቴአትር ቤቱ ከ1983 ዓ.ም እስከ 1985 ዓ.ም በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ሥራውን አቋርጦ የነበረ ቢሆንም በ1986 ዓ.ም እንደገና ተከፍቶ በአዲስ አበባ መስተዳድር ማስታወቂያና ባህል ቢሮ ስር ከሶስቱ የአዋቂ ቴአትር ቤቶች ጋር በባህል መምሪያ ስር ይተዳደር ነበር ፡፡ ቴአትር ቤቱ ለህፃናትና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በማቅረብ የተቋቋመ አትራፊ ያልሆነ በመንግስት የሚደገፍ ብቸኛ የህፃናት የኪነ ጥበብ ማዕከል ነው፡፡
የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን ህፃናት መብት ኮንቬንሽን መሠረት በማድረግ እንዲሁም አምራች ዜጋ የሆነውን ወጣት ትውልድ በሥነ ጥበብና በዲሲፒሊን ታንፀው እንዲያድጉና ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትመኘውን ጠቃሚ ዜጋ ለማፍራት ታስቦ የተመሠረተ ብቸኛ የመንግስት ተቋም ነው ቴአትር ቤቱ በህፃናትና ወጣቶች ህይወትና ዕድሜ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን በስፋትና በብዛት ለሚመለከታቸው ተመልካቾች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
እስካሁን ካቀረብናቸው የጥበብ ሥራዎችም የህፃናት ቴአትሮችን፣የወጣቶችቴአትሮች፣ ፓፔት ቴአትሮች፣ የተለያዩ ጭውውቶች፣ ብዛት ያላቸው ይዘታቸው በሀገራችን ታሪካዊ ቦታዎች፣መናፈሻዎችና አእዋፋት፣ ሙዚየሞችና የሀገራችን ህዝቦች አኗኗርና ባህል፣ ወግ የመሳሰሉት ላይ የሚያተኩር በቴአትር ቤቱ ተቀርፀውና ተቀነባብረው የሚቀርቡ ፊልሞችና አውሮፓዊ ፊልሞችን እንዲሁም የሀገራችን የብሔርብሔረሰቦችን ህዝቦችን ማንነት ባህልና ወግ የውዝዋዜ ስልቶችን በጉልህ የሚያንፀባረቁ ዘፈኖች እያቀረበ ይገኛል፡፡
ቴአትር ቤታችን ከመደበኛ ዕቅድ በተጨማሪ በመልካም አስተዳደርና በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የንቅናቄ ስራዎችን በከተማችን ውስጥ ያሉትን የልማት ስራዎችን ለማፋጠንና ህብረተሰቡ የሚሰራቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች ገንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ የሬዲዮ ድራማዎችና የሬዲዮ ስፖቶች፣ መዝሙሮች ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉትን የንቅናቄ ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የቴአትር ቤቱ አድራሻ
አራት ኪሎ
ስልክ ቁጥር
+251.111-22-38-06
+251.111-22-59-44
+251.111-22-32-92
ፋክስ
+251.111-23-49-49
ፖ.ሳ.ቁ 8751

Addis Ababa Culture and tourism is a division of Addis Ababa City Administration